የኢትዮጵያ ሰማዕታት ቀን 82ኛ ዓመት የመታሰቢያ ስነ ስርዓት በዛሬው እለት ተካሂዷል።

0
708

መታሰቢያ ስነ ስርዓቱ በተለይ 6 ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሰማእታት አደባባይ ከማለዳው ጀምሮ በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ሰማእታት አደባባይ የመታሰቢያ ስነ ስርዓት ላይም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ሌሎች ድርጅቶች ተወካዮች የአበባ ጉንጉን የማስቀመጥ ስነስርአት አካሂደዋል።
የመታሰቢያ በዓሉ በጣልያን ወረራ ጊዜ በጀነራል ግራዝያኒ ትእዛዝ በሶስት ቀናት ብቻ የተጨፈጨፉ 30 ሺህ ዜጎች የሚታሰቡበት ነው።
በ1929 ዓ.ም ለጣሊያን ንጉሳዊ ቤተሰብ አንድ ልዑል በመወለዱ ምክንያት በጀኔራል ግራዚያኒ ትዕዛዝ በቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግስት የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሱቲ 6 ኪሎ ግቢ ደስታውን ለማክበር የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን እንዲሰበሰቡ ትዕዛዝ በመተላለፉ በርካታ ህዝብ ታዳሚ ሆኗል።
በዚህ ቅጽበት ታዲያ ጀኔራል ግራዚያኒን ጨምሮ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ለፋሽስቱ ያደሩ ባንዳዎችና መኳንቶች፣ የፋሽስቱ ባለስልጣናትና ወታደሮች በተገኙበት አስደንጋጭ የሚባለው አደጋ ተከሰተ።
ለፋሽስቱ መገዛት ያመናል ያሉት አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ኢትዮጵያውያን የያዙትን የዕጅ ቦንብ ወደ ግራዚያኒ ወረወሩ፥ እናም በዚህ አደጋ እራሱ ጀኔራል ግራዚያኒ እና በርካታ የፋሽስቱ ባለስልጣናት የመቁሰል አደጋ ደረሰባቸው።
ይህን ጊዜ ለግራዚያኒ የኢትዮጵያ ህዝብ መቼም ቢሆን በግዛቱ ስር ሊሆን እንደማይፈቅድ ማረጋጋጫ ሳይሆንለት አልቀረም።
ይህን አደጋ ለመበቀልም በዚያው ዕለት በግቢው ውስጥ የነበሩትን ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን፣ ቀጥሎም የተማሩ ወጣቶችን፣ የጦር መኮንኖችና የኃይማኖት አባቶችን፣ እየለቀሙ ያለርህራሄ በጅምላ ጨፈጨፉ።
የካቲት 12 ቀን 30 ሺህ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትን የተቀበሉበትን ቀን ለማሰብ በአዲስ አበባ ከተማ የሰማዕታት ሐውልት እንዲቆምላቸው ተደርጎ ቀኑ በየአመቱ እየታሰበ ይውላል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here