በደቡብ ወሎ ዞን በጫጉላ ሥነ ሥርዓት ላይ በፈነዳ ቦምብ የሙሽራና ሚዜ ሕይወት አለፈ

0
506

በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ በጫጉላ ሥነ ሥርዓት ላይ በፈነዳ ቦምብ ሙሽራውን ጨምሮ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት የሰው ኃይል የሥራ ሂደት አስተባባሪ ኢንስፔክተር ሰይድ ስበር ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ቀበሌ 024 በሚገኘው የሙሽራው መኖሪያ ቤት ትናንት ከቀኑ 8፡00 ላይ ነው ።
“ሙሽራና ሙሽሪት ጥር 14 ቀን 2011 የሰርግ ሥነ -ሥርዓታቸውን በመፈፀም ባዘጋጁት የጫጉላ ሥነ ሥርዓት ላይ ከሚዜዎቻቸው ጋር በመጫወት ላይ ሳሉ ድንገት አደጋው ተከስቷል “ብለዋል።
ሚዜዎች ሙሽራው የታጠቀውን ቦምብ በመነካካታቸው ድንገት ፈንድቶ ሙሽራውና የአንድ የወንድ ሚዜ ህይወት ማለፉን ተናግረዋል።
ሙሽራው የታጠቀው ቦምብ ሕገወጥ መሆኑን ኢንስፔክተር ሰይድ ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ በሕጋዊ መንገድ የያዘውን የጦር መሣሪያ ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ይዞ ከመገኘት እንዲቆጠብም አስገንዘበዋል።
አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በሠርግና በበዓላት ወቅት ያለአግባብ በሚያዝና በሚተኮስ ጥይት ኅብረተሰቡን ስጋት ላይ እየጣለ ነው ።
ያለአግባብ የጦር መሣሪያዎች በሚይዙ ግለሰቦች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here