በኢትዮጵያ የሞባይል ተጠቃሚዎች ይፋዊ ቁጥር በ25 ሚሊዮን ገደማ አሽቆለቆለ

0
683

በሀገሪቱ ብቸኛው የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች አቅራቢ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም  ባወጣው ሪፖርት የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር 39.5 ሚሊዮን መሆኑን አስታውቋል።
ኢትዮ ቴሌኮም  ይፋ ያደረገው ሪፖርት የ2011 ዓ .ም. በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸምን የዘረዘረ ነው። ኩባንያው በሪፖርቱ ከሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሌላ የመደበኛ ስልክ፣ የዳታ እና ኢንተርኔት ደንበኞችን ቁጥር ይፋ አድርጓል። መንግስታዊው የቴሌኮሚዩኒኬሽን ኩባንያ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ በሰጠው መግለጫ የሞባይል ተጠቃሚዎቹ ብዛት 64.4 ሚሊዮን መድረሱን ገልጾ ነበር። በዘጠኝ ወር ልዩነት ውስጥ በወጣው ሪፖርት ላይ ግን የተጠቃሚዎቹ ቁጥር በ25 ሚሊዮን ያህል አሽቆልቁሎ ታይቷል።
በተጠቃሚዎች ቁጥር ላይ ሰፊ ልዩነት መፈጠሩን የሚቀበሉት የኢትዮ ቴሌኮም የኮሚዩኒኬሽን ኤክዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር ወይዘሪት ጨረር አክሊሉ ምክንያቱ እስከ ሰባት ዓመታት ከአገልግሎት ውጪ የነበሩ የሞባይል ቁጥሮች በአጠቃላይ የተጠቃሚዎች ብዛት ስር እንዳይካተቱ በመደረጋቸው ነው ብለዋል። “የተጠቃሚዎችን ቁጥር በተመለከተ ዘንድሮ ከሁለት ዓመት በላይ ተጠቃሚ የሌላቸውን ቁጥሮች እንደገና አገልግሎት (recycle) ላይ አውለናል። ያ ማለት አጣርተን አገልግሎት ላይ ያልዋሉ ቁጥሮችን ከዚህ ዳታ አውጥተናል ማለት ነው” ሲሉ ምክንያቱን አብራርተዋል።
የቀደመው አሰራር “ከዓለም አቀፍ መስፈርት አንጻር ትክክል አይደለም” የሚሉት ወይዘሪት ጨረር አሁን አገልግሎት ላይ ያሉ ቁጥሮች ብቻ እንዲካተቱ መደረጉ ስለ ሞባይል ተጠቃሚዎች “ትክክለኛ መረጃ” ለማግኘት ይረዳል ብለዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ላይ ያልዋሉ 18 ሚሊዮን የሞባይል ቁጥሮችን “መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ” ለሽያጭ ማቅረቡንም ተናግረዋል። ቀሪዎቹ አምስት ሚሊዮን ገደማ ቁጥሮችም ማጣራት እየተደረገባቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ደንበኞች በእንደዚህ አይነት አሰራር የቀደመ ቁጥራቸውን እንዳያጡ ካለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ ጀምሮ ለአንድ ወር ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸው እንደነበር ወይዘሪት ጨረር ገልጸዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ውጭ ሀገር ለሚጓዙም ሆነ በተለያየ ምክንያት የሞባይል ቁጥራቸውን ለረጅም ጊዜ ለማይጠቀሙ ደንበኞች “የቁጥሬን አቆዩልኝ” አገልግሎት ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ መጀመሩንም ኃላፊዋ አስታውሰዋል። አንድ ደንበኛ ቁጥሩን እስከ አምስት ዓመት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ማቆየት እንደሚችልም ጠቁመዋል። ይህን አገልግሎት ለመጠቀም የሚሻ ደንበኛ በየዓመቱ 109 ብር መክፈል ይጠበቅበታል።
በዛሬው የኢትዮ ቴሌኮም የስራ አፈጻጸም ሪፖርት የመደበኛ ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥርም ቀንሶ ታይቷል። ኩባንያው ከዘጠኝ ወር በፊት የመደበኛ ስልክ ደንበኞቹ 1.2 ሚሊዮን መሆናቸውን የገለጸ ቢሆንም በዛሬው ሪፖርቱ ቁጥሩ ወደ 1.14 ሚሊዮን ወርዷል። ከመደበኛ ስልክ ወደ ሞባይል አገልግሎት የተዛወሩ ደንበኞች አገልግሎቱን ማቋረጣቸው ለቁጥሩ መቀነስ ምክንያት መሆኑን ወይዘሪት ጨረር አስረድተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል እና መደበኛ ስልክ ደንበኞቹ ቁጥር ቢቀንስም የዳታ እና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ብዛት ግን ባለፈው ዓመት ከነበረው መጨመሩን በዘገባው ተመልክቷል። በግንቦት 2010 ዓ. ም. የኢትዮ ቴሌኮም የዳታ እና ኢንተርኔት ደንበኞች ብዛት 16 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ቁጥራቸው በ3.5 ሚሊዮን መጨመሩን የኩባንያው ሪፖርት አሳይቷል። የዳታ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ድርጅቱ በመንፈቅ ዓመት ውስጥ ካስገባው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ ሁለተኛውን ከፍተኛ ድርሻ ይዟል።
ከድርጅቱ 16.71 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ከተንቀሳቃሽ ስልክ የተገኘው ሲሆን ይህም 63 በመቶውን ይሸፍናል። ከገቢው ዝቅተኛውን ድርሻ የያዘው ከዓለም አቀፍ ጥሪ የተሰበሰበው ሲሆን ከአጠቃላይ ገቢው 5.5 በመቶውን ብቻ እንደሚሸፍን ኢትዮ ቴሌኮም ገልጿል። በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የድምጽ ጥሪዎች ላይ በሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ኩባንያው ሊያገኘው የሚገባው ገቢ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ኢትዮ ቴሌኮም በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።
ምንጭ ፦DW Amharic

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here