መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መኪኖችን ዕድሜ ሊገድብ ነው

0
477

ኢትዮጵያ ያገለገሉ መኪኖች ወደ ገበያዋ እንዳይገቡ የሚገድብ ሕግ በማዘጋጀት ላይ ትገኛለች።
በአንድ አመት ውስጥ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀው ሕግ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በላይ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ያግዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከተመረቱ አምስት አመት ያስቆጠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ አገሪቱ ገበያ እንዳይገቡ ሊያግድ የሚችል ሕግ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።
ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ሶስት ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ ኮሚቴ ያዘጋጀውን ጥናት በትራንስፖርት ሚኒስቴር በኩል ለኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር አቅርቧል።
ኮሚቴው ከኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ገቢዎች ሚኒስቴር እና የገንዘብ ሚኒስቴር የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ ነው።
በኢትዮጵያ ተሽከርካሪ የሚገጣጥሙ ተቋማትን መደገፍ፣ የትራፊክ አደጋን እና የከባቢ አየር ብክለትን መቀነስ እንዲሁም በታክስ አማካኝነት አገሪቱ የምታገኘውን ገቢ ማሳደግ ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የመጨረሻ አስተያየት እንዲሰጡበት የቀረበውን ጥናት በቅርበት የሚያውቁ ባለሙያ ከ5 አመት በላይ ያገለገሉ መኪኖች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዳይገቡ የማገድ ሐሳብ መቅረቡን አረጋግጠዋል።
ለገንዘብ ሚኒስቴር ቀርቧል በተባለው ጥናት መሠረት ከተመረቱ እስከ ሁለት አመት የሆናቸው ተሽከርካሪዎች 5 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጣልባቸዋል።
ይኸው የታክስ አይነት ከተመረቱ ከሁለት እስከ ሶስት አመታት ላስቆጠሩ ተሽከርካሪዎች አስር በመቶ፤ ከሶስት እስከ 5 አመት ለሚሆናቸው ደግሞ 20 በመቶ እንዲሆን ይደረጋል።
የመኪኖቹ ዕድሜ ከፍ ባለ ቁጥር የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔውም ከፍተኛ ጭማሪ ያሳያል። ዕድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ አስር አመታት የሆነ ተሽከርካሪዎች የሚጣልባቸው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን 100 ፐርሰንት ይሆናል።
# DW Amharic

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here