አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ የተመድ ሰራተኞች ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል

0
348

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቋሚነትና በጊዜያዊነት የሚሰሩ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ ሰራተኞች ጾታዊ ጥቃት እንዳጋጠማቸው ተነገረ።
ይህንን ያስታወቀው ተመድ አዲስ ባወጣው ሪፖርት ሲሆን፥ ድርጊቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ያጋጠመ መሆኑ ነው የተገለጸው።
ሪፖርቱን ተከትሎም የተመድ ዋና ጸሐፊ የሆኑት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በመጥቀስ፥ እርምጃ መውሰድ የሚገባን ወቅት ላይ ደርሰናል ብለዋል።
በተጨማሪም ድርጊቱ ተቋሙ ካስቀመጣቸው መርሆች አንጻር የሚጣረስ በመሆኑ፥ ምሳሌ ሊያደርገን የሚችል አቋም መውሰድ አለብን ሲሉ ተደምጠዋል።
በኦንላይን በተሰበሰበው በዚህ ጥናት በተቋሙና በኤጀንሲዎቹ ውስጥ የሚሰሩ 34 ሺህ 364 ግለሰቦች ተሳትፈዋል።
በጥናቱም 21 ነጥብ 7 በመቶዎቹ ተሳታፊዎች ወሲባዊ የሆኑና ያልተገቡ ቀልዶችን ሲያስተናግዱ፥ 14 ነጥብ 2 በመቶዎቹ የሰውነት አቋማቸውን በተመለከተ ዘለፋ ማስተናገዳቸውን አስፍረዋል።
እንዲሁም 13 በመቶዎቹ ደግሞ ወሲባዊ በሆኑ ውይይቶች ላይ ያለፍቃደኝነት እንዲሳተፉ ሙከራ እንደተደረገባቸው ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም 10 ነጥብ 9 በመቶዎቹ ባልተገባ መልኩ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን በመጠቀም ጉንተላ ሲደርስባቸው፥ 10 ነጥብ 1 በመቶዎች ያለፍቃዳቸው መተሻሸት እንደገጠማቸው ተናግረዋል።
በጥናቱ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሰዎች ጾታዊ ትንኮሳ የደረሰባቸው በቢሯቸው አካባቢ መሆኑን ሲጠቅሱ፥ 17 ነጥብ 1 በመቶዎቹ ከስራ ጋር በተያያዙ በሚዘጋጁ ማህበራዊ ሁነቶች መሆኑን አንስተዋል።
ሁለት ሶስተኛ የሚሆነውን ጾታዊ ጥቃት አድራሾች ወንዶች መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ ሴቶች ናቸው ተብሏል።
ሆኖም ጥቃት ካስተናገዱ ሦስት ሰዎች መካከል አንዱ ግለሰብ ላይ ብቻ ነው እርምጃ መውሰዱ የተሰማው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here