በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር 4 የንግድ ማስተላለፊያ ኬላዎች ሊከፈቱ ነው

0
514

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ህጋዊ የድንበር ላይ የንግድ ልውውጥ ለማስጀመርና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ 4 የንግድ ማስተላለፊያ ኬላዎችን ለመክፈት የመለየት ስራ ማጠናቀቁን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
በአገራቱ በዜጎች መካከል ድንበር ላይ የተጀመረው የንግድ ልውውጥ የጉምሩክ አሰራርን ጨምሮ ህጋዊ ስርዓት እንዳልተበጀለት ሲነገር ቆይቷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም የዛልአንበሳ ድንበር፤ የጉምሩክና ተያያዥ ስርዓቶች እስኪስተካከሉ ተብሎ በቅርቡ መዘጋቱ ይታወሳል።
እናም ይህንን ሁኔታ በመለወጥ የአገራቱን ምጣኔ ኃብታዊና የንግድ ግንኙነት ህጋዊ በሆነ መንገድ ለማስቀጠል የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ነው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ዛሬ ያስታወቀው።
በዚህም መሰረት በጉምሩክ ኮሚሽን አማካኝነት የንግድ ማስተላለፊያ (ትራንዚት) ፕሮቶኮል የተዘጋጀ ሲሆን ሰነዱም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚመራው አገር አቀፍ ኮሚቴ መቅረቡን በኮሚሽኑ የህግ ማስከበር ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ ገልፀዋል።
የንግድ ማስተላለፊያ (ትራንዚት) ፕሮቶኮሉ በቅርቡ በአገራቱ ፀድቆ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።
በፕሮቶኮሉ መሰረትም በአገራቱ መካከል የገቢና የወጪ ዕቃዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አራት የንግድ መተላለፊያ ኬላዎች በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ ለመክፈት ዝግጅቱ ተጠናቋል።
ከሚከፈቱት አራት የትራንዚት ኬላዎች ውስጥ ራማና ዛላምበሳ ተጠቃሽ ናቸው።
እንደ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉጌታ ማብራሪያ በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ የሚከፈቱት አራቱ ኬላዎች ጊዜያዊ ሲሆኑ የንግድ እንቅስቃሴው ስፋት እየታየ እና ህገወጥነትንም ለመቆጣጠር ጭምር እንደአመቺነቱ ተጨማሪ ኬላዎች ይከፈታሉ።
ለኬላዎቹ የሚያስፈልጉ የሎጀስቲክና የሰው ኃይል ምደባ ስራ መጠናቀቁን ምክትል ኮሚሽነር ሙሉጌታ ገልጸዋል።
የአገራቱን ምጣኔ ኃብታዊ ግንኙነት ለማጠናከር የጉምሩክ ኮሚሽን በምፅዋና በአሰብ ሁለት ቢሮዎችን እንደሚከፍትም ጠቁመዋል።
ምንጭ፡- ኢዜአ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here