በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ተሰብስቧል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

0
496

በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር መሰብሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ።
እስካሁን ባለው ሂደት በትረስት ፈንዱ አማካኝነት 12 ሺህ 9 መቶ ዳያስፖራዎች መዋጮ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የ2011 ዓ.ም አገራዊ በጀትን በአስጸደቁበት ወቅት ዳያስፖራው በአገሩ ልማት ላይ እንዲሳተፍ በቀን የ1 ዶላር መዋጮ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ዳያስፖራው ለጠቅላይ ሚነስትሩ የሰጠው ምላሽ አጥጋቢ እንዳልሆነ ሲነገር ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች በሰጡት ገለጻ አስካሁን ባለው ሂደት ዳያስፖራው በቀረበለት ፈንድ አማካኝነት 1 ነጥበ 9 ሚሊዮን ዶላር አዋጥቷል።
በመዋጮውም 12 ሺህ 900 ዳያስፖራዎች እንደተሳተፉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህም ውስጥ 10 ሺህ 300 የሚሆኑት በአሜሪካ የሚኖሩ ናቸው።
1ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላሩ ከእነዚህ በአሜሪካ ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች መሰብሰቡን አክለዋል።
በአሜሪካ ካሉ ግዛቶች መካከል ሜሪላንድና ካሊፎርኒያ እንደቅደም ተከተል ከፍተኛ መዋጮ የተገኘባቸው አካባቢዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በዓለም ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዳያስፖራዎች ቢኖሩም መዋጮው እምብዛም ያልሆነበት ምክንያት መተማመኑ ባለመፈጠሩ መሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትሩ አስገንዝበዋል።
የሚዋጣውን ነገር በሚታይ ነገር ላይ በማዋል መተማመንን ለመፍጠር እንደሚሰራ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፈንዱ የተሰበሰበው ገንዘብ ግን 10 ሚሊዮን ዶላር አስኪደርስ ጥቅም ላይ እንደማይውል ገልጸዋል።
ይህ የሚሆነውም በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መካካል ፍትሃዊ ክፍፍልን ለመፍጠር መሆኑንም ጠቁመዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here