የህግና ፍትህ ስርዓትን መረጃ በአንድ ቦታ ማግኘት የሚያስችል የመረጃ ቋት ይፋ ሆነ

0
706

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግና ፍትህ ስርዓትን መረጃ በአንድ ቦታ ማግኘት የሚያስችል የመረጃ ቋት ይፋ አደረገ፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ የመረጃ ቋቱ ከ1934 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ የወጡ ህግና ደንቦችን ህብረተሰቡ በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያስችል ነው።

አሰራሩ ህብረተሰቡ የፍትህ ህግና ስርዓት እንዲያውቅ ከማድረግ በተጨማሪም ሰበር ሰሚ ችሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኝ ይረዳልም ነው ያለው።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ እንደሚሉት፥ አገልግሎቱ ህብረተሰቡ ስለ ፍትህና ህግ ስርዓቱ ጠንቅቆ እንዲያውቅና ሁሉም ሰው በያለበት አገልግሎቱን እንዲያገኝ ያግዛል።

አገልግሎቱ ያለበይነ መረብ መጠቀም የሚቻል ሲሆን÷ የመረጃ ቋት መተግበሪያውን የእጅ ስልክ ወይም ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ላይ በመጫን መጠቀም እንደሚቻልም ነው የተገጸው፡፡
ይህ አገልግሎት ህጎችና ደንቦች በየጊዜው ሲሻሻሉ ለመከታተል የሚያስችል ሲሆን÷ ህጎችና ደንቦች ሲሻሻሉ የመረጃ ቋቱ በራሱ መረጃዎችን እንደሚያሻሽልም ታውቋል፡፡አሁን ላይ ሃገሪቱ እያስተናገደች ያለውን ለውጥ ለመደገፍ ከማገዙም በተጨማሪ፥ ህብረተሰቡ ስለ ፍትህ ስርዓቱ የሚኖረውን እውቀት የሚያሰፋ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ባለፉት ጊዜያት የተላለፉትን 16 ሺህ ያህል ሰበር ሰሚ ችሎቶች ለህብረተሰቡ ለማስተላለፍ አስቸጋሪ የነበረ ሲሆን፥ አዲሱ አሰራር ግን ይህን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ነው የተባለው።
የፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫ ኤጀንሲም በዛሬው ዕለት 19 አገልግሎቶችን በበይነ መረብ ለመስጠት የሚያስችለውን አሰራር ይፋ ማድረጉ ነው የተገለጸው፡፡

አዲሱ የሰነዶች ማረጋገጫ ኤጀንሲ አሰራር ደንበኞቹ ባሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን፥ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ መሆኑም ተነግሯል፡፡
ውክልና ሽያጭና ስጦታ ከአገልግሎቶቹ መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን፥ በዘርፉ የሚያጋጥመውን የማጭበርበር ሂደትም ያስቀራል ተብሏል።
ቀደም ሲል በቀን ከ20 እስከ 30 ያህል ሰዎች አገልግሎቱ ይሰጥ የነበረ ሲሆን፥ አዲሱ አሰራር በቀን እስከ 7 ሺህ ያህል ደንበኞችን ማስተናግድ የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል፡፡
መተግበሪውን ከተቋሙ ድረ ገጽ በማውረድ ከአሁኑ ሰዓት ጀመሮ መጠቀም እንደሚቻልም ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here