ሁለት ጊዜ በታወጁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ሳቢያ ሆቴሎች ገበያ አጥተው፣ ስብሰባዎች በ70 በመቶ ቀንሰው ነበር

0
518

በኢትዮጵያ የሆቴልና የቱሪዝም ዘርፉ ለሁለት ዓመታት ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱ ሲገለጽ በተለይም ሁለት ጊዜ በታወጁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ሳቢያ ሆቴሎች ገበያ አጥተው ቢቆዩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያንሰራሩና ከተፅዕኖ እያገገሙ እንደመጡ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች የዘርፍ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢንያም ብስራት ሐሙስ ታኅሳስ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በሁለት ዓመታት ውስጥ ለ14 ወራት በዘለቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳቢያ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ሆቴሎች ችግር ውስጥ ከርመዋል፡፡ በመሆኑም ቀድሞ የነበረው የጎብኝዎች የቆይታ ጊዜ ወደ 3.5 ቀን ዝቅ እንዳለና ጭራሹኑ ሆቴሎች ባዷቸውን ለመቆየት የተገደዱባቸው ወራት እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡ በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅን ተከትሎ ኤምባሲዎች ያወጧቸው የጉዞ ማሳሰቢያዎችና ክልከላዎች ትልቅ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡
እንዲህ ባሉ ምክንያቶች በየሆቴሎች ይካሄዱ የነበሩ ስብሰባዎችም በከፍተኛ ደረጃ ቀንሰው እንደቆዩ ማኅበሩ ያወጣቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በ2009 ዓ.ም. 55,650 ስብሰባዎች መካሄዳቸው ሲታወቅ፣ በ2010 ዓ.ም. ግን ወደ 16,909 ዝቅ ማለቱን ማኅበሩ አጣቅሷል፡፡ በአንፃሩ በ2008 ዓ.ም. ከ79 ሺሕ በላይ ስብሰባዎች መስተናገዳቸውም ታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት በ2010 ዓ.ም. የተስተናገዱት ስብሰባዎች ከ2009 ዓ.ም. አኳያ የ70 በመቶ ቅናሽ ያስተናገዱ ሲሆን፣ የ2009 ዓ.ም. ስብሰባዎችም ከ2008 ዓ.ም. አኳያ የ30 በመቶ ቅናሽ እንደታየባቸው መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ስብሰባዎችን በብዛት በማስናገድ ረገድ ከአፍሪካ በአምስተኛ ደረጃ እንደምትቀመጥ ሲጠቀስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ሩዋንዳና ግብፅ ቀዳሚዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ ከከተሞች አኳያም ኬፕታውን፣ ጆሀንስበርግ፣ ኪጋሊና ማራኬሽ ከአዲስ አበባ በመቅደም ባለፈው ዓመት በርካታ ስብሰባዎችን አስተናግደዋል፡፡

እንዲህ ያሉ እውነታዎችን ያስተናገዱት የአዲስ አበባ ሆቴሎች በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪው ውስጥ መሻሻል እየታየና ገበያውም እያንሰራራ መምጣቱን አቶ ቢንያም ጠቅሰው፣ ይህም ሆኖ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጆቹ በፊት ወደ ነበሩበት ደረጃ ለመመለስ ብዙ እንደሚቀራቸው አብራርተዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here