አንበሳ አውቶቡስ ውስጥ የተወለደው ‹‹የሕፃን አንበሳው›› 1ኛ ዓመት ልደት ተከበረ

0
701

አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ወስጥ የተወለደውና እናቱ “#አንበሳው” የሚል ስም ያወጡለት ብላቴና 1ኛ ዓመት ልደት በዓል በአንበሳ አውቶቢስ ውስጥ በዛሬው እለት ተከበረ፡፡
“አንበሳው” ዓምና በዚች ቀን ለረጅም ዘመን ያገለገለ ዳፍ 24 ቁጥር አንበሳ አውቶቡስ ውስጥ የተወለደ ብላቴና ነው፡፡
እናትየው ወይዘሮ በየነች ተስፋዬ ይባላሉ ፤ ዓምና በዛሬው ዕለት በአውቶቡሱ ተሳፍረው ሲንቀሳቀሱ ምጥ ያፋፍማቸዋል፤ ጫጫታም በአውቶቡሱ ይፈጠራል ፤ በዚህ ጊዜ ሹፌሯ ወይዘሮ ተዘራሽ ታምሩ ምን ተፈጥሮ ይሆን ብለው የሚያሽከረክሩትን አውቶቡስ ቀኛቸውን በመያዝ ወደ ዳር አውጥተው ያቆሙታል፤ የተፈጠረውን ነገር ለማየት ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ወይዘሮ በየነች ምጥ እንዳፋፋማቸው ይመለከታሉ፡፡ ሾፌሯ በመቀጠልም ተሳፋሪውን እንዲወርድ አድርገው የተገኘውን ጨርቅ ከጋረዱ በኋላ ባላቸው ልምድ ማዋለድ ይጀምራሉ፡፡ ወይዘሮ በየነችም በሰላም ወንድ ልጅ ይገላገላሉ፡፡
ተሳፋሪዎች በመውረድ መተባበር ብቻ ሳይሆን ወይዘሮ ተዘራሽ እንግዴ ልጁን ለመቁረጥ ምላጭ ሲጠይቁ ሁሉም ኃላፊነት ተሰምቶት ለመግዛት በመሯሯጥ ባስ ካፒቴኗ ያገር ምላጭ ይቀርብላቸዋል፡፡
እንግዴ ልጁን ቆርጠው ሕፃኑን ቡራዩ ጤና ጣቢያ በወሰዱት ጊዜ ሐኪሞች በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሆነ ያረጋግጡላቸዋል፡፡
ብላቴናው ይኸው አንድ ዓመት ሞልቶት አንበሳ አውቶቢስ ድርጅት አስፈላጊውን ወጪ ሸፍኖ ዛሬ ሞቅ ባለ ሁኔታ በአውቶቡስ ውስጥ ልደቱ ተከብሮለታል፡፡
መልካም ልደት ለአንበሳው
ምንጭ ፦Anbessa City bus Service Enterprise

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here