1 ሺህ 550 ተማሪዎች ለኩረጃ ሲሉ ስማቸውን ለውጠዋል

0
567

ከሰሞኑ ከወደ አማራ ክልል የተሰማው የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል፤ በባለፈው የትምህርት ዘመን ከናሙና ዞኖችና ትምህርት ቤቶች በተገኘ መረጃ ተማሪዎች ለኩረጃ ይመቻቸው ዘንድ ከጎበዝ ተማሪዎች ጋር በማመሳሰል ስማቸውን በፍርድ ቤት አስለውጠዋል ።
በተያዘው የትምህርት ዘመንም ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥም የክልሉ ትምህርት ቢሮ የቀየሰው አንዱ ዘዴ ተማሪዎቹ ስማቸውን እንዳይለውጡ እግድ ማስጣል ነበር።
በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዓለምእሸት ምህረቴ አንዳንድ ተፈታኞች ለኩረጃ ሲሉ ስማቸውን ከጎበዝ ተማሪዎች የስም ፊደል ጋር እያመሳሳሉ በፍርድ ቤት እየቀየሩ አንደሆነ ጠቅሰው ይህን በተመለከተ ትምህርት ቢሮው ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ደብዳቤ መፃፉንም አውስተዋል።
ደብዳቤው ድርጊቱ ላልተገባ ዓላማ እየዋለና በጎበዝ ተማሪዎች ስነ ልቦና ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቅሶ ፈተናዎቹ ከኩረጃ የፀዱ ይሆኑ ዘንድ የፈተናው ምዝገባ እስኪጠናቀቅ ስም መቀየር የሚከለክል የህግ አሰራር ተግባራዊ እንዲደረግ ይጠይቃል።
ከደብዳቤውም ጋር በ2010 ዓ. ም ከተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተሰበሰቡና ከጎበዝ ተማሪዎች ስም ጋር የተመሳከሩ 1550 ተማሪዎችን ስም ዝርዝር ያለበት 37 ገፅ አያይዟል።
ይሄንን መነሻ በማድረግ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጊዜያዊ መፍትሄ ይሆናል በማለት በክልሉ ለሚገኙ 13 ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ጊዜያዊ የስም ለውጥ የሚከለክል እግድ እንደፃፈ ይናገራሉ።
እነዚህ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችም በስራቸው ለሚገኙ ወረዳ ፍርድ ቤቶች ተመሳሳይ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የተጠቀሰውን ችግር ለመፍታት ሲባልም ፍርድ ቤት የስም ለውጥ እግዱ የ8ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ክፍል የፈተና ምዝገባ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ እንዲቆይ የሚያዝ ነው።
“ፍርድ ቤቱ ይህንን ትዕዛዝ ያስተላለፈው ዜጎች በፈለጉት ስም የመጠራት መብታቸውን ለመገደብ ተፈልጎ ሳይሆን በክልሉ የገጠመውን የፈተና ስርዓት ተግዳሮት ለማቃለል ነው” ይላሉ አቶ ዓለምእሸት።

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሆኑት አቶ ተፈራ ፈይሳ ቢሮው የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ የሚያከናውናቸው በርካታ ተግባራት ቢኖሩም እግዱ የስም ለውጥ በማድረግ የሚደረግን ኩረጃ ለመቀነስ የተጠቀሙት አማራጭ እንደሆነ ይናገራሉ።
ላለፉት 5 ዓመታት የሚጠቀሙበት የትምህርት ክትትል ስርዓት እንዳላቸው የሚናገሩት ኃላፊው በክልሉ ኩረጃ ያን ያህል ሰፊ ባይሆንም ተማሪዎች በራሳቸው ተማምነው እንዲሰሩ ለማድረግና ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ይህንን እግድ ጨምሮ ሌሎች መፍትሔዎችን እየወሰዱ እንደሚገኙ ይገልፃሉ።

ጉዳዩ በክልሉ የሚገኙ ተማሪዎችን የማይወክል ቢሆንም በራሳቸው የማይተማመኑ ተማሪዎች የጎበዝ ተማሪዎችን ስም እየፈለጉ ስም የሚቀይሩ ግን አሉ፤ በመሆኑም ኩረጃ በትምህርት ጥራት ላይ እንቅፋት በመሆኑ እንደ አንድ ወሳኝ መፍትሔ ባይሆንም ችግሩን ለመፍታት በማሰብ ይህን አማራጭ እንደተጠቀሙ ይገልፃሉ።
ተማሪዎቹ ለኩረጃ ሲሉ ስማቸውን ስለመቀየራቸው ማረጋገጫ ከየት አገኛችሁ ያልናቸው ኃላፊው በየዓመቱ ትምህርት ቢሮው ግምግማ እንደሚያካሂድ ጠቅሰው በዚህም መሰረት ቁጥራቸውን ለጊዜው በውል ባያስታውሱትም የተወሰኑ ተማሪዎች ለኩረጃ ሲሉ ስማቸውን እንደሚለውጡ ከደረሳቸው መረጃ ተረድተዋል።
አቶ ተፈራ እንደሚሉት በተለይ ምዝገባ በሚካሄድባቸው ወቅት የስም ለውጦች ተበራክተው ይታያሉ፤ በመሆኑም ይህንን ለመከላከል ለ3 ወራት የሚዘልቅ (ከህዳር – የካቲት) የስም ለውጥ እግድ ለማድረግ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር እንደተስማሙ ያስረዳሉ።
“ትምህርት ቢሮው ይህንን መፍትሄ ትክክለኛ መፍትሄ ነው ብሎ ባያምንም ለትልቁ መፍትሄ አጋዥ ይሆናል” ይላሉ አቶ ተፈራ።
ይህም ግለሰቦች በፈለጉት ስም የመጠራት መብት ለመጣስ ሳይሆን ችግሩን ለመፍታት በሚል ከፍርድ ቤቱ ጋር በተደረገ ቀና ስምምነት እንደሆነ ያሰመሩበት ጉዳይ ነው።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ በበኩላቸው ምንም እንኳን በቅንነት ታስቦ በጊዜያዊ መልክ እግድ የተጣለ ቢሆንም እግዱ የስም ለውጥ መብትን ይጥሳል በሚል ከህግ ባለሙያዎችና ሚዲያዎች ትችት እንደተሰነዘረባቸው ይናገራሉ።
እንደ አንድ የፍትህ መስሪያ ቤት፤ ከሌላ አካል ቅሬታና አስተያየት እስከሚመጣ ለምን ጠበቃችሁ? ቀድሞስ ጉዳዩን እንዴት አላሰባችሁበትም? ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው ዳይሬክተሩ “ያለውን ጊዜያዊና መሰረታዊ ችግር መነሻ በማድረግ ታስቦ የተፃፈ ሲሆን ይህም ስህተት ሆኖ ተገኝቷል” ይላሉ።
“ቢሮው ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንጂ መታገዱ ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታው አይችልም፤ በህግ የተረጋገጠ የግለሰብ መብት በጊዜያዊም ቢሆን የሚገድብ በመሆኑ እንዲሁም በአስተዳደር የሚሰጥ ትዕዛዝ ለሌላ ያልተገባ ልምድ ሊሆን ይችላል በማለት ደብዳቤው ስህተት መሆኑን ፍርድ ቤቱ አምኗል” ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
በመሆኑም በትናንትናው ዕለት የእግዱ የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ የመስሪያ ቤቶቹን ተዋረድ በጠበቀ መልኩ እግዱን የሚሽር ደብዳቤ ማሰራጨታቸውን ነግረውናል።ይሁን እንጂ የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊውን ባነጋገርናቸው ወቅት እግዱ እንዲነሳ የሚጠይቀው ደብዳቤ እንዳልደረሳቸው ነግረውናል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ አማርኛ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here