ከአፍሪካ ጦር ኃይል አቅም ግብፅ በቀዳሚነት ፣ኢትዮጵያ በስድስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ ሪፖርት አመለከተ

0
690

‹‹ግሎባል ፋየርፓወር›› የተሰኘው የአሜሪካ ተቋም እ.ኤ.አ. ከ2006 ጀምሮ አገሮችን ከኢኮኖሚያዊ አቋማቸው በመንተራስ የወታደራዊ አቅም ደረጃቸውን ይፋ ያደርገ ፡፡ ተቋሙ ወታደራዊ ትንታኔዎችን በማውጣት ዘመናዊ ጦር የታጠቁ 136 አገሮችን ያነፃፀር  ሲሆን፣ ከእነዚህ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ በመሆን በደረጃ ተመድባለች፡፡

ተቋሙ ባስቀመጣቸው 55 መስፈርቶች ፣ደረጃዎችና መደቦች መሠረት ከአፍሪካ ኢትዮጵያ በግብፅ፣ በአልጄሪያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በናይጄሪና በአንጎላ ተቀድማ  ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተደልድላለች፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ደረጃ የያዘችው ከቀደመው ደረጃ ወደ ታች ወርዳ ሲሆን፣ በዓለም ደረጃ ንፅፅር ተደረጎባቸው ደረጃ ከተቀመጠላቸው 136 አገሮች ውስጥም በ51ኛ ረድፍ ላይ ትገኛለች፡፡

በአፍሪካ አንደኛ በዓለም 12ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ግብፅ፣ 875 ሺሕ ተጠባባቂ ጦሯን ጨምሮ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ የሠራዊት አባላት እንዳሏት ዓመታዊ የመከላከያ በጀቷም ከ4.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት አገር እንደሆነች በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ ከ1132 በላይ የጦር አውሮፕላኖች ያሏት ግብፅ፣ 309 ተዋጊ አውሮፕላኖች እንዳሏት ተጠቅሷል፡፡ 269 ሔሊኮፕተሮች፣ 5,000 ያህል ታንኮች፣ ከ15 ሺሕ በላይ ብረት ለበስ የጦር ተሽከርካሪዎች፣ ከ1,200 በላይ ተወንጫፊ ሮኬቶች አሏት ተብሏል፡፡ ከዚህ ባሻገር ስድስት ባህር ሰርጓጆች፣ ሁለት አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦችና ከ320 ያላነሱ የባህር ኃይል የውጊያ አሃዶች የገነባች አገር ተብላለች፡፡

ኢትዮጵያ ተጠባባቂ ጦር ከሌላቸውና የባህር በር አልባ ከሆኑ አገሮች ተርታ የምትመደብ ሲሆን 80 የጦር አውሮፕላኖች ፣ ከእነዚህም 48 ተዋጊና ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች መሆናቸውን 42 የመጓጓዣ፣ 14 የሥልጠና፣ እንዲሁም 33 ሔሊኮፕተሮች እንዳሏት ከእነዚህ ውስጥም ስምንቱ የውጊያ መሆናቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪ 800 የውጊያ ታንኮች፣ 800 ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፣ 183 የሮኬት ተወንጫፊዎችና ሌሎችም ወታደራዊ መሣሪያዎችን በመታጠቅ በአፍሪካ ኃያል ከሚባሉ አገሮች ተርታ መግባቷን፣ ለመከላከያ የምትመድበው ዓመታዊ በጀት ከ340 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ እንዳላት ከሚገመተው ከ105 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ውስጥ ለጦር ኃይል አባልነት ሊመለመል የሚችል 40 ሚሊዮን  የሰው ኃይል እንዳላት ሪፖርቱ አመላክቶ፣ ከዚህ ውስጥ 24 ሚሊዮን ሕዝብ ለውትድርና አገልግሎት ብቁ መሆኑን አስፍሯል፡፡ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ለውትድርና ዕድሜው ብቁ የሚሆነው ሕዝብ ብዛት ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅት ያለው መደበኛ የአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል ብዛት ግን 162 ሺሕ እንደሆነም ግሎባል ፋየርፓወር አሥፍሯል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here