0
575

ፊትና ኋላ – ለአእምሮ ጨዋታ

(በዲያቆን ዳንኤል ክብረት)

በታሪክ ትርክት ውስጥ ፊትና ኋላ የቱ ነው?
‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ› የሚል በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚቀነቀን ብሂል አለ፡፡ መልእክቱ ግልጽ ነው፡፡ ‹የጥንቱ ከሌለ የዛሬውና የነገው አይኖርም፤ የጥንቱ ለዛሬውና ለነገው መሠረት ነው› የሚል ነው፡፡ እንዴው ቀለል ያለ ነገር እናንሳ፡፡ በታሪክ ትርክ ውስጥ ፊትና ኋላው የትኛው ነው? የፊቱ የትኛው ነው? የኋላውስ? የኋላው ይቀድማል ወይስ የፊቱ?
ዐፄ ምኒልክ ባረፉ ጊዜ እረኛ ገጠመው የሚባል ግጥም አለ፡፡
ምኒልክ አለፈ ሄደ ምትለኝ
ፊትም አልነበረ ኋላም አይገኝ
የሚል፡፡ የዚህ ግጥም ገጣሚ ‹ፊትም አልነበረ፣ ኋላም አይገኝ› ይላል፡፡ ፊት የሚለውን ‹ነበረ› ከሚለው ኃላፊ ግሥ ጋር፣ ኋላ የሚለውን ደግሞ ‹አይገኝ› ከሚለው የወደፊቱን አመልካች ጋር ነው ያቀረበው፡፡ ስለዚህም ፊት ከኋላ ይቀድማል ማለቱ ነው፡፡ ልክ እንደ ተፈጥሮ፡፡
ሌላም ግጥም አለ፡፡
በሉ እናንተም ሂዱ እኛም ወደዚያው ነው
ድሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው፤
የሚል የለቅሶ ግጥም ነው፡፡ ኑሮን እንደመንገድ፣ ሰው እንደ ተጓዥ፣ ሞትን እንደ ወሳጅ ቆጥሮ የተገጠመ ነው፡፡ ፊትና ኋላ ነው ሲል – ቀዳሚና ተከታይ መሆኑን ያመለክታል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስም ‹ፊተኞች ኋለኞች፣ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ› ይላል፡፡ ይህ የተተረጎመበት ግእዙ ‹ደኀርት ይከውኑ ቀደምት ወቀደምት ይከውኑ ደኀርት› ይላል፡፡ ፊተኞችን – ቀደምት፤ ኋለኞችንም ደኀርት ብሏቸዋል፡፡ ስለዚህም ከኋላ ፊት ይቀድማል ማለት ነው፡፡
እናም አባባሉ ‹የፊቱ ከሌለ የለም የኋላው› መሆን ያለበት አይመስላችሁም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here