ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ነገ ጠዋት አዲስ አበባ ይገባሉ

0
594

የቀድሞ የቅንጅት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ነገ ጠዋት አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለት ጊዜ ለእስር ከተዳረጉ በኋላ የተፈቱትና መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉት የሕግ ባለሙያዋ ወ/ሪት ብርቱካን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት በመንግሥት ጥሪ ተደርጎላቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በ1992 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ በግል ተወዳዳሪነት መሳተፍ የጀመሩት ወ/ሪት ብርቱካን፣ በ1998 ዓ.ም. የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ነበሩ ፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን በፖለቲካ ተሳትፏቸው ዕውቅና ከማግኘታቸው በፊት፣ በ1993 ዓ.ም. አቶ ስዬ አብርሃ፣ በሙስና ተጠርጥረው ከታሰሩበት የወንጀል ክስ በነፃ እንዲሰናበቱ በሰጡት የፍርድ ውሳኔ ታዋቂነት ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡

ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. በተደረገው ሦስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ካሸነፉ ተወዳዳሪዎች አንዷ ነበሩ፡፡ በ1999 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከሌሎች የቅንጅት አመራሮችና አባላት ጋር ታስረው በይቅርታ መፈታታቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን  ወ/ሪት ብርቱካን‹‹ይቅርታ አልጠየኩም›› የሚል መግለጫ በማውጣታቸው በታኅሳስ ወር 2001 ዓ.ም. በድጋሚ  ለሁለት ዓመታት በማረሚያ ቤት ታስረው ተፈተዋል፡፡

ወ/ሪት ብርቱካን ከእስር እንደተፈቱ ወደ አሜሪካ ሄደው ላለፉት ሰባት ዓመታት ቆይተዋል፡፡ በቆይታቸውም በታዋቂው ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሕዝብ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

በመንግሥት ጥሪ ወደ አገር ቤት ጠቅልለው ከተመለሱ ምናልባትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር፣ ወይም የፌዴራል የመጀመርያ ወይም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ተደርገው ሊሾሙ እንደሚችሉ ከወዲሁ ትንበያዎች እየተሰሙ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here