‹‹መሲ ጋሪ ዖልቴ፣ ጋሩማ፣ ኦ ማሲንቆ. . . ›› የማሲንቆው አውራ ለገሠ አብዲ (1931-2011)

0
650

ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ የተቆራኛትን ማሲንቆን በኦሮምኛ ዜማ ሲያጫውታት ኅብረተሰቡንም ሲያጫውት ኖሯል፡፡በቀድሞ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ሰላሌ አውራጃ ያያ ቃጫማ በተባለ ስፍራ በ1931 ዓ.ም. የተወለደው ድምፃዊው ለገሠ፣ማሲንቆ መጫወትን የተማረው የአባቱ የቅርብ ወዳጅ በነበረው ዝነኛው የማሲንቆ ተጫዋች ወሰኑ ዲዶ ነበር፡፡ በልጅነቱ በተለያዩ በዓላት በሠርግና በማኅበር ላይ በመገኘት ያዜም እንደነበር ይወሳል፡፡ በ1950ዎቹ መጀመርያ ከወሰኑ ጋር ወደ አዲስ አበባ መምጣቱ የሚወሳው ድምፃዊው በ17 ዓመቱ ክብር ዘበኛን በመቀላቀል በኦርኬስትራው፣ በሀገር ፍቅር ቴአትር፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት (ብሔራዊ)፣ በማዘጋጃ ቤት ከማገልገሉ ባሻገር ከባህል ሙዚቀኞች ከነሀብተሚካኤል ደምሴ ጋር በመሆን በተለያዩ የምሽት ክለቦች ሠርቷል።‹‹ማሲንቆን እንደ ሰው ያነጋግራታል›› የሚባልለትና በግጥምና ዜማ ደራሲነት የሚታወቀው ከያኒው ለገሠ ከ12 በላይ ሥራዎቹን በሸክላ፣ በካሴትና በቪሲዲ አሳትሟል፡፡ስመጥር ካደረጉት የኦሮምኛ ዘፈኖች ውስጥም ያ ቦና ያቦና፣ ጂጂቱ፣ ኢያ ሀንዳቆ እና ኮቱ ያ ጂጋኮ ቀዳሚ ይጠቀሳሉ። በሮምና ቶኪዮ ኦሊምፒክ ወርቃማ ድል ያስመዘገበውን አበበ ቢቂላና በሜክሲኮ ኦሊምፒክ ማራቶን ተመሳሳይ ድል የተቀዳጀውን ማሞ ወልዴ እንዲሁም ታዋቂውን የረዥም ርቀት ሯጭ ዋሚ ቢራቱ የሚያወድስ ዜማም አቀንቅኖል።የማሲንቆው አውራ ድምፃዊ ለገሠ አብዲ ባደረበት ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ  ጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በ 84 አመቱ አርፎል፡፡

ለገሰ አብዲ በኦሮመኛ የባህል ሙዚቃ ታሪክ ስሙ በግንባር ቀደምትነት ሲታውስ ይኖራል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here