የኢሕአዴግ ጉባዔ አዲስ የኢሕአዴግ ምክር ቤት እንደሚመሠርትና የኢሕአዴግን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር እንደሚመርጥ ተገለጸ።

0
568
 1. በኢሕአዴግ ጉባዔ የሚመሠረተው አዲስ ምክር ቤት የግንባሩን ሊቀመንበር ይመርጣል ተባለ።
  መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የሚጀመረው የኢሕአዴግ ጉባዔ አዲስ የኢሕአዴግ ምክር ቤት እንደሚመሠርትና፣ ምክር ቤቱም በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የኢሕአዴግን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር እንደሚመርጥ ተገለጸ፡፡
  የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የኢሕአዴግ ጉባዔ ከሚወያይባቸው አጀንዳዎች በተጨማሪ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ምርጫ በማካሄድ እከእያንዳንዱ የኢሕአዴግ ጉባዔ የሚያገለግል ምክር ቤት ይመሠርታል፡፡
  ይህ ምክር ቤት ከእያንዳንዱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ በእኩል የሚውጣጣ እንደሚሆን የተናገሩት ኃላፊዋ፣ በግንባሩ መተዳደርያ ደንብ መሠረትም የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ምክር ቤቱ እንደሚመርጥ ጠቁመዋል፡፡
  ወ/ሮ ፈትለወርቅ ምክር ቤቱ በሚያካሂደው ምርጫ በሥራ ላይ የሚገኙት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ደመቀ መኰንን ምትክ ሌላ ይመርጣል? ወይስ ሁለቱ ሊቃነ መናብርት ይቀጥላሉ የሚለውን ግን አላብራሩም፡፡
  የኢሕአዴግ ከፍተኛ ኃላፊዎች ግን አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ጊዜውን በመጨረሱ፣ አዲስ የምክር ቤት ምርጫ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
  በግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የኢሕአዴግ ምክር ቤት ከአንድ ዘመን እስከሚቀጥለው ጉባዔ ድረስ ግንባሩን በበላይነት እንደሚመራ፣ አሁን በሥራ ላይ ያለው ምክር ቤት የሥልጣን ዘመን በዚህ ጉባዔ እንደሚያበቃ አስረድተዋል፡፡
  ይህ ማለት ግን በሥራ ላይ ያሉት የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላት በድጋሚ አይመረጡም ማለት እንዳልሆነ የገለጹት ኃላፊዎቹ፣ በድጋሚ የሚመረጡና አዳዲስ አባላት ግንባሩን እስከ ቀጣዩ ጉባዔ ድረስ የመምራት ኃላፊነት በጉባዔው እንደሚወሰንላቸው ተናግረዋል፡፡
  በዚህ አግባብ የሚመሠረተው አዲሱ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር እንደሚመርጥ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን የሚደረገው የሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ምርጫ የተለመደ ሥርዓት (Procedure) ከመሆኑ ውጪ ነባሮቹን ሊቃነመናብርት በድጋሚ እንደሚመርጥ ጠቁመዋል፡፡

የኢሕአዴግ ጉባዔ ከሚያወያይባቸው አጀንዳዎች መካከል ያለፉት አምስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሪፖርት፣ ያለፉት ሦስት ዓመታት የሥራ አፈጻጸም ግምገማና ቀጣይ አቅጣጫን መወሰን ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም አጋር ድርጅቶች የኢሕአዴግ አባል መሆን በሚችሉበት ሁኔታና ኢሕአዴግን ማዋሀድ በሚመለከት የሚቀርብ ሰነድ ላይ መምከርና ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጥ የሚሉም አሉበት፡፡ በዚህ ጉባዔ አንድ ሺሕ አባላት በድምፅ የሚሳተፉ መሆኑ ታውቋል፡፡ የኢሕአዴግ መሥራች አባላት በታዛቢነት ያለ ድምፅ በጉባዔው ተሳታፊ እንደሚሆኑ፣ ሌሎች 900 የአገር ውስጥና የውጭ እንግዶች ደግሞ የጉባዔውን መክፈቻ እንዲከታተሉ ተጋብዘዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here